ክርስትና (የልጅነት ጥምቀት)

ወደ ክርስትና እምነት የሚያስገባ ቅዱስ ምሥጢር
መቼ
በየሰንበት ከቅዳሴ በፊት
የሚወስደው ጊዜ
በግምት አንድ ሰዓት
ተሳታፊዎች
ወላጆች፣ የክርስትና አባት/እናት እና ልጁ
ስለ ክርስትና
አስቀድመን በሥጋ ከእናትና ከአባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” በማለት (ዮሐ 3፥3 እና 6) ስለ ልጅነት ጸጋና ስመ ክርስትና አስተምሯል፡፡ እንዲሁም “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ...” (ሮሜ 8፥15-16) እና “ለተቀበሉት ሁሉ ... ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጥቶአቸው” (ዮሐ 1፥11-13) ተብሎ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ሁለት ልደታት አሉን፤ መጀመሪያ ከሥጋ እናትና አባታችን፣ ሁለተኛ ከእግዚአብሔር። ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን እንዲሆን ያስፈልጋል (ገላ 3፥26፣ ቲቶ 3፥5፣ 1 ጴጥ 1፥23)።
የልጅነት ጥምቀት በምን ይፈጸማል?
ልጅነት የምታሰጠው ጥምቀት አንዲት ናት (ኤፌ 4፥4-5)፣ ነገር ግን በሦስት ዋና መንገዶች ታገለግላለች። የውኃ ጥምቀት በተባረከ ውኃ እና በሥላሴ ስም በካህናት ይፈጸማል፤ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከእግዚአብሔር እንወለዳለን (ዮሐ 3፥3-6)። ውኃው በጸሎት ሲባረክ የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ ይሆናል እና በእምነት የሚጠመቅ ከውኃና ከመንፈስ ይወለዳል። ጥምቀት የእግዚአብሔር ጸጋ መገለጫ ነው፤ ስለዚህ ድሀ ሰው እንኳ ውኃ አለው ስለዚህ በውኃ መጠመቅ ይገባል። የመንፈስ ጥምቀት (ሉቃ 3፥16፣ ሐዋ 1፥5፣ ሐዋ 2፥1-4፣ 1 ቆሮ 12፥13) እና የደም ጥምቀት የሰማዕታት ጥምቀት ናቸው፣ በመሞታቸው ልጅነት ይቀበላሉ።
ጥምቀት እንዴት ይፈጸማል?
ተጠማቂው ንዑሰ ክርስቲያን ከሆነ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርቶችን ተምሮ እምነቱ የተመሰከረለት መሆን አለበት። ሕጻናት የሆኑ እንደሆኑ ግን ለሕጻናቱ የክርስትና እናትና አባት ሊሆኑ የመጡት ሰዎች ስለሕጻናቱ እምነት መስክረውላቸው እንዲጠመቁ ይደረጋል። በሚጠመቅበት ጊዜ በውሃ ውስጥ ሶስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለት አለበት ፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምሳሌ ነውና። ተጠማቂው የሚጠመቀው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው (ማቴ 28 ፥ 19)። ተጠማቂዎች ባለትዳሮች ከሆኑና ቤተሰብም ካላቸው ሁሉም ተምረው አምነው በአንድነት መጠመቅ አለባቸው። ከተጠመቀ በኋላ መቁረብ (ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል) ይገባል። ይህ ካልሆነ ጥምቀቱ ህያው አይሆንም።
እንዲያጠምቁ ስልጣን ያላቸው ከክህነት ደረጃዎች ውስጥ ኢጲስቆጶስና ቀሳውስት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማጥመቅ ስልጣንን የሰጠው ለአስራ አንዱ ሐዋርያት ብቻ ስለሆነ ነው (ማቴ 28፡19)፡፡ ዲያቆናት እንዲያጠምቁ አልተፈቀደላቸውም (ማቴ 28፡19 እና ፍት ነገ አንቀጽ 3)። ክህነት በሌለው ሰው የተከናወነ ጥምቀት እንደ እጥበት እንጂ እንደ ጥምቀት አይቆጠርም፡፡ በዚህ መንገድ "የተጠመቀ" ሰው ልጅነት የምታስገኘዋን እውነተኛዋን ጥምቀት መጠመቅ አለበት፡፡ ጥምቀት በመድፈቅ ወይም በመንከር ነው እንጂ በመርጨት (በንዝሐት) አይፈጸምም፡፡ ምሳሌውን፣ ምስጢሩንና ሥርዓቱን ያፋልሳልና፡፡ ጥምቀት ማለት መነከር ማለት ስለሆነ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ውኃ ውስት ገብቶ በመውጣት ይከናወናል (ማቴ 28፡19)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም የተገለጠው በመንከር የተከናወነው ጥምቀት ነው፡፡
በሐዋርያት ሥራ ላይ "ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና (ሐዋ 8፡38-39)" በሚለው ቃል ውስጥ "ከውኃ ከወጡ በኋላ" የሚለው የሚያመለክተው ጃንደረባው የተጠመቀው ውኃ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነው፡፡ "እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡4-5 ቆላ 2፡12)" በሚለው ቃል ውስጥ መቀበር መቃብር ውስጥ መግባትን፣ ትንሣኤ ደግሞ ከመቃብር መውጣትን እንደሚያመለክት ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ (በመነከር) መውጣትን ይጠይቃል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለለም (ቲቶ 3፡5)" እንዲሁም "አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ (ሐዋ 22፡16)" ተብሎ ለሳውል በተነገረው ቃል ውስጥ "መታጠብ" ሰውነትን በሙሉ ነውና ጥምቀትም በመነከር ይከናወናል፡፡ በአራቱም ወንጌላት የጌታችን ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ በመውጣት መሆኑ ተጽፏል፡፡ "ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ (ማቴ 3፡16)" በሚለው ቃል ውስጥ "ከውኃ ወጣ" የሚለው የጌታችን ጥምቀት የተከናወነው በመነከር እንደነበር ያሳያል፡፡ መረጨት ወይም ማፍስስ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን አይጠይቅምና፡፡ በተጨማሪም በሥጋ መወለድ በእናት ማኅፀን ውስጥ ቆይቶ መውጣትን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ "ከውኃና ከመንፈፈስ ቅዱስ መወለድም" እንዲሁ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን (መነከርን) ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ነው ጥምቀት "ዳግመኛ መወለድ" የተባለው (ዮሐ 3፡3)፡፡


ስመ ክርስትና (የክርስትና ስም)
ስም አንድ ሰው ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ነው። ሰው ከእናትና ከአባቱ ሲወለድ ስም እንደሚወጣለት ሁሉ በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድም ስም ይወጣለታል፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ስሞች ሊኖሩት ይችላል። አባትና እናት የሚያወጡለት ስም የተጸውኦ ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የሚወጣለት ስም ደግሞ የክርስትና ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ይገኝበታል፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሰው ክርስቲያን ሲባል እምነቱ ደግሞ ክርስትና ይባላል። ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ወገን የሆነ ማለት ነው። በመሆኑም በክርስቶስ አምነን በሥላሴ ስም መጠመቃችንን የሚገልጸው ስም ስመ ክርስትና ይባላል። ስያሜውም ተጠማቂው ከተጠመቀበት ዕለት ጋር ተያይዞ ሊሰየም ይችላል። በመንፈሳዊ አገልጎት ስንሳተፍ ስመ ክርስትናችንን እንጠቀማለን፡፡ የክርስትና ስም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት ያለው ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አብራምን አብርሃም፣ ያዕቆብን እስራኤል፣ ሰምዖንን ጴጥሮስ፣ ሳውልን ጳውሎስ እንዲባል እንዳደረገው ያለ ነው፡፡
ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ
በሐዋርያት ስብከት ያመኑና በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁሉ ይጠመቁ ነበር (የሐ ሥራ 16፡ 15 1ቆሮ 1፡15) ። በኋላ ግን ወላጆቻቸው ሊያስተምሯቸው ቃል እየገቡ ልጆቻቸውን ወንዶችን በአርባ ሴቶችን በሰማንያ ቀናቸው ማጥመቅ ተጀመረ። ለዚህም መሠረቱ የእስራኤል ልጆች በተወለዱ ወንድ በአርባ ሴት በሰማንያ ቀናቸው ወላጆቻቸው መባዕ (ስጦታ) ይዘውላቸው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ በእስራኤልነት (የዜግነት) መዝገብ እያስመዘገቡ የተስፋዋ ምድር ከነዓን ባለመብቶች (ወራሾች) ያደርጓቸው እንደነበረ ነው (ዘሌ 12፡1-10)፡፡
አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ፣ ሔዋንም በተፈጠረች በ80 ቀኗ ወደ ርስታቸው ገነት እንደገቡ ሕጻናትም በ40 እና በ80 ቀናቸው ተጠምቀው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ወደሆነችው ወደ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ህጻናት ወላጆቻቸው እንዲሁም ክርስትና እናት ወይም አባት ሃይማኖታቸውን ሊያስተምሯቸው ሃላፊነት ወስደው የክርስትና አባት ወይም እናት በተጨማሪ ቃል ገብተው ክርስትና በመነሳት (በመጠመቅ) የወላጆቻቸውን ርስት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ። ከአርባ እና ከሰማንያ ቀን በኋላ የሚመጡ ተጠማቂዎች ግን ሃይማኖታቸውን ተምረው ካመኑ በኋላ በማንኛውም የዕድሜ ክልል መጠመቅ ይችላሉ ። በሕይወት እስካሉ ድረስ መቸም ቢሆን ከመጠመቅ የሚያግዳችው ነገር የለም ።
የክርስትና አባትና እናት
በ40 እና በ80 ቀናቸው ለሚጠመቁ ሕጻናት ስለ እኝነታቸው ባለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ የክርስትና አባትና እናት እንዲኖራቸው ያደረጉት በ4ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው ኢጲስ ቆጶስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ናቸው። ዓላማውም መንፈሳዊ ዝምድናን (አበ ልጅነትን) ማጠናከሪያ መንገድ ነው። በአበ ልጅነት የተዛመዱ ሰዎች በጋብቻ መዛመድ አይችሉም። በሥጋ የተዛመዱ ከ7ተኛ የዝምድና ሐረግ በኋላ መጋባት የሚፈቀድ ሲሆን በአበ ልጅ ግን የተዛመደ ግን የቁጥር ገደብ የለውም (ፈጽሞ መጋባት አልተፈቀደለትም)፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሥጋ ዝምድና ይልቅ ክብር የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ዝምድና መሆኑን ነው።
ከክርስትና አባትነትና እናትነትን የሚከለክሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የሥጋ ዝምድና ያላቸው፣ የጋብቻ ዝምድና ያላቸው፣ ዕድሜያቸው ለማስተማር ለማሳመን ያልደረሰ፣ እምነት ትምህርት ችሎታ የሌላቸው፣ እምነታቸው ከተጠማቂው ጋር ተመሳሳይ ያልሆነ ናቸው፡፡ የጾታ ሁኔታ በተመለከተ ወንድ ወንድን ሴት ሴትን ያነሣል እንጂ ወንድ ሴትን፣ ሴት ወንድን ክርስትና ማንሣት አይፈቀድላቸውም፡፡ የክርስትና አባትና እናት ክርስትና ያነስዋቸው ልጆች በሥጋ ከወለድዋቸው ልጆች ሳይለዩ፣ ሕጻናቱ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸው ቃል ይገባሉ። በገቡት ቃል መሠረት በተግባር የመተርጎም ኃላፊነት አለባቸው።
ማዕተብ (ክር) ማሰር
ማዕተብ የሚለው ቃል ዐተበ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አመለከተ ማለት ነው። ስለዚህ ማዕተብ ማለት ምልክት ማለት ነው። በሃይማኖት አምነው ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የሚሰጥ ምልክት (መታወቂያ) ወይም ማኅተም ነው። ስለ ማዕተብ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል። በብሉይ ኪዳን የነበሩ አባቶች ለእምነታቸው መገለጫ ምልክት ነበራቸው። ለምሳሌ ለአበ ብዙኃን አብርሃም ግዝረት ተሰጥቶት ነበር (ሮሜ 4፡13 ፡ ዘፍ 17፡9-14)። ማዕተብ ክርስቶስ በገመድ መታሰሩንና መጎተቱን የሚያስታውስ ምልክትም ነው፡፡ "ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና (1ኛ ጴጥ 2:21)።" እንተባለ የክርስቶስን መከራ እናስብበታለን (ዮሐ 18፡12-24)
ማዕተብ በሦስት ዓይነት ቀለም መሆኑ የሦስትነት (የሥላሴ) ምሳሌ ነው። ሦስቱ ክሮች ደግሞ በአንድ ተገምደው መሠራታቸው የአንድነቱ ምሳሌ ነው። ክርስቲያን ማዕተብ በማሰሩ ስለ ክርስቲያንነቱ ሳያፍር ይመሰክርበታል፤ አጋንንትን ድል ይነሣበታል፡፡ ተጸልዮበት ተባርኮ የሚታሠር ነውና ከቤተክርስቲያን በረከት ያገኝበታል፡፡ ማዕተብ ማሰርን ያስጀመረው ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ክርስቲያኖችን ከመናፍቃን ለመለየት ማዕተብ ያስርላቸው እንነበር በመጻሕፍት ተጽፏል፡፡
የሚታይ አገልግሎት፤ የማይታይ ጸጋ
በምስጢረ ጥምቀት የሚታይ አገልግሎት ተጠማቂው ውሃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ሲል፤ ሥርዓተ ጸሎቱ ሲከናወን፤ ተጠማቂው ነጭ ልብስ ሲጎናጸፍ፣ ማዕተብ ሲያስር ወይም ሲታሰርለት ወዘተ... ነው፡፡ ይህ የዓይኖቻችን የምናየው ነው፡፡ በምስጢረ ጥምቀት የሚሰጥ የማይታይ ጸጋ ደግሞ ውኃው ወደ ማየ ገቦ ሲለወጥ፣ ተጠማቂው የእግዚአብሔር ልጅነት ሲያገኝ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ፣ ንጽሕናና ቅድስና ሲሰጥ ነው፡፡ ምስጢረ ጥምቀት በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚሰጥበት ልዩ ምስጢር ነው፡፡
