እምነታችን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን

ከዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ የክርስትና ወግና ባህሎች አንዱ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ
ኢትዮጵያ የጁዲዮ የክርስትና እምነትና ባሕል ያላት ጥንታዊት አገር ስትሆን የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት የሚግኙባት ነች። አስገራሚ ታሪክ፣ ድንቅ ሥልጣኔዋ፣ባሕልና ሃይማኖታዊ የሆነው የሕዝቧችዋ አኗኗር ልዩ ያደርጋታል። በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው "የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፣እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።" (ዘፍ. 2፥13) በዳዊት መዝሙር ደግሞ "ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች" (መዝ. 67(68)፥31)። ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ በብዙ የታሪክ መዛግብትና መጽሐፍት ላይ ስለ ኢትዮጵያ ተዘግቧል። በተጨማሪ ታሪካዊና አርኬኦሎጂካል ግኝቶች የሚያስገርሙ ሃቆችን ስለ ኢትዮጵያ እየገለጹ ነው። ኢትዮጵያ የራስዋ የሆነ ፊደል ከነአጻጻፉና ሥርዓቱ ጋር ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ነች።
ጥንታዊ የግሪክ ባለ ቅኔዎች፣ ገጣሚዎችና የታሪክ ጸሐፊዎች ስለኢትዮጵያ ብዙ ጽፈዋል፤ ከነዚህ መካከል ሆሜር ስለአገሪቱና ስለሕዝቧ ሲገልጽ "እንከን የሌለባቸው ዘሮች" ሲል ሔሮዶቱስ ደግሞ የኢትዮጵያን የመልክዐ ምድር አቀማመጥን እንዲህ ሲል ገልጾታል፣ "ከግብፅ በስተደቡብና የቀይ ባሕር አካባቢን ይዞ እስከ ሕንድ ወቂያኖስ የሚጠጋ ግዛት ነው" ስለሕዝቧም ሲናገር "የረጅም እድሜ ባለፀጎችና እውነተኛ የሆኑ ሕዝቦች ናቸው"ብሏል።
በብሉይ ኪዳን ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ለመጎብኘት ወደ የኢየሩሳሌም ያደረገችውን ጉዞ በ1ኛ ነገ. 10፥1-13 ተጽፎ ሲገኝ በኢትዮጵያውያንም ዘንድ ይህ ጉዞ ብሉይ ኪዳን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ያደረገና፤ የንጉሥ ሰለሞንና የንግሥት ሳባ ልጅ የሆነው ቀዳማዊ ምኒሊክ ጽላተ ሙሴን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደረገ ነው ተብሎ ይታመናል።
በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት የገባው በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና ሌሎች ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። (ሐዋ. 8፥26-36) ላይና በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ "የኢትዮጵያው ጃንደረባ ጥምቀት በዓለም የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ" ብሎታል በተጨማሪም ሩፊኖስ ቀጥሎም በቴዎድሬት፣ሶቅራጦስና ሶዝሜን ታሪክ ዘጋቢዎች ይህንን ታላቅ ሁኔታ ዘግበውታል።
ከዚያን ጊዜ በኋላ የአይሁድ እምነትና ሥርዓተ አምልኮ የሕዝቧ እምነትና የቀን ተቀን ኑሮ መመሪያ ሆኗል። በቀዳማዊ ምኒሊክ የተመሰረተው የአክሱም ሥርወ መንግሥት ተብላ ትታወቅ ነበር። በተጨማሪ ብዙ የታሪክ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ነፃ መንግሥት የተመሰረተው ከ 4,522 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። የዛሬይቱ አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ዋና መዲና፣የሥልጣኔ መገኛና የክርስትና እምነት መወለጃ እንደሆነች ዛሬ የሚታዩት የሕዝቧ ኣኗኗርና ሃይማኖታዊነት፣ ታሪካዊ ቅርሶችዋ፣የቆሙት ሐውልቶችዋና ልዩ ልዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ሲመሰክሩ አክሱም አሁንም ዋነኛ የሃይማኖት መንጸባረቂያ ቅድስት ቦታ ነች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንቶችና የተማሩ ቀሳውስቶች ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከሰላሳ ሺህ በላይ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀሳውስቶችና ወደ አርባ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ያላት አገር ስትሆን በዚህም ከምሥራቃውያን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ አገሮች በምዕመናን ብዛት የቀዳሚነትን ሥፍራ ይዛለች።
በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት አመጣጥ
የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና ሌሎች ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። (ሐዋ. 8፥26-36) ላይና በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ "የኢትዮጵያው ጃንደረባ ጥምቀት በዓለም የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ" ብሎታል በተጨማሪም ሩፊኖስ ቀጥሎም በቴዎድሬት፣ሶቅራጦስና ሶዝሜን ታሪክ ዘጋቢዎች ይህንን ታላቅ ሁኔታ ዘግበውታል። ይሁን እንጂ ክርስትና የመንግሥት እምነት ሆኖ በኤጲስ ቆጶስ ደረጃ መመራት የጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይተረካል። ይኸውም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ፍሬሚናጦስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አድርጎ የሾመው በዘመነ አብርሃና አፅብሃ ጊዜ ነው። ንጉሥ ኤዛና በገንዘቦቹ ላይ የነበሩትን የጨረቃ ሥዕልን ቀይሮ የመስቀል ምልክት በማድረግ በዓለም ከነበሩት ነገሥታቶች መካከል ቀድምትነትን ቦታ አግኝቷል። በ356 ዓ.ም. አርያናው ንጉሥ ኮንስታንትዩስ ለአክሱም ንጉሥ ሲጽፍ "ጳጳሱ ፍሬሚናጦስ የክርስትናን እምነት አጥፊ ስለሆነ ወደ ሮም ተይዞ ይላክ" ብሎ ነበር። ነገር ግን ይህ ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝለት ቀርቷል። ቅዱስ ፍሬሚናጦስ በኋላ በኢትዮጵያውያን ኣባ ሰላማ (የሰላም አባት) ከሳቴ ብርሃን (የብርሃን ገላጭ) እየተባለ ሲታወቅ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የጳጳሳት መጠሪያ የሆነውን አቡን የሚባለው አጠራር ማለትም (አባታችን) ተቀብሎ ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ብቻ ትቀበላለች እነርሱም የኒቅያው ጉባኤ (325 ዓ.ም.) የኤፌሶን ጉባኤ (381 ዓ.ም.) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (431 ዓ.ም.) ናቸው።
ምንኩስናና ገዳማት በኢትዮጵያ
ክርስቲያናዊ የሆነ ገዳማዊ ኑሮ በኢትዮጵያ ማበብ የጀመረው የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱ ብሔራዊ እምነት ሆኖ በነገሥታቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው። የግብፃዊው የቅዱስ አንጦኒዮስን ገዳማዊ ሥርዓት የተከተለ በ 479 ዓ.ም. ወደ ሀገሪቱ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን አስፋፍተውታል።
ስለዚህ ነው ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ ወርቃማው ተብሎ የሚታወቀው። በነዚህ ዘመናት ውስጥ ብዙ የስብከት ወንጌል ሥራዎች ተስፋፍተዋል፣ ልዩ ልዩ መንፈሣዊ ሥራዎችና ጽሑፎች የተከናወኑበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ ያሉ ገዳማት የምዕራባውያንን ባሕል በመካከላለኛው ክፍለ ዘመን እንዲስፋፋና እንዲጠበቅ እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትም የእውቀትና የሥልጣኔ ማዕከል በመሆን ሥነ ጽሑፎችን፣ ሥነ ሕንፃን፣ ቅኔዎችን፣ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና መንፈሣዊ ትምህርቶች እንዲዳብሩ አድርገዋል። በ5ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የቅድሴ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና ውዝዋዜዎችን በመፍጠር ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ ለጆሮ ክፍተኛ ጣዕም ያለውን የምስጋናና የጸሎት ሥርዓት ያላትና የምትጠቀም በዓለም ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን አድርጓታል።
መንፈሳዊ ሕይወት
ጸሎት
መደበኛ ጸሎት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊ ሲሆን፣ ለተለያዩ የቀን ሰዓታት የተወሰኑ ጸሎቶች አሉ።
ጾም
ጾም በስፋት ይከናወናል፣ በዓመት ውስጥ ከ250 ቀናት በላይ የጾም ቀናት እንደ መንፈሳዊ ሥርዓት ይከናወናሉ።
ምጽዋት
ምጽዋትና ለችግረኞች መንከባከብ የክርስትና እምነትና ፍቅር አስፈላጊ መግለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
አሥራት በኩራት
በኩራት
- በኩር (የመጀመሪያ) ከሚለው ቃል ነው። በኩራት የእግዚአብሔር ነው - ዘፀ 23፡19፣ ዘሌ 23፡10-11
- በኩራት መስጠት ማለት እግዚአብሔርን በነገሮቻችን ሁሉ ማስቀደም ማለት ነው - ዘኁ 3፡13፣ ዘዳ 15፡19
- የበኩራት ስጦታ ትዕዛዝ ነው - ዘፀ 13፡2፣ ዘዳ 26፡2
- የመጀመሪያውን ስንሰጥ ያለን ነገር ይባረክልናል - 1ሳሙ 2፡20-21
አሥራት - ዘፍ 14፡20፣ ዕብ 7፡4-5
- አሥራት በብሉይ ኪዳን ከአስር አንድ እጅ ማለት ነው - ዘፍ 28፡22
- አሥራት በአዲስ ኪዳን ግን ከአስር አንድ እጅ ባለፈ በዘራኸው ልክ ነው - 2ቆሮ 9፡6-7
- አሥራት የእግዚአብሔር ንብረት ነው - ሚል 3፡8-10
- አሥራት የሚሰጡ (የሚያስገቡ) ሰዎች በታማኝነት የእግዚአብሔርን ንብረት መልሰው ለእርሱ የሚሰጡ ናቸው - ዘዳ 14፡22-23
- አሥራትን በማስገባት (በመስጠት) ውሰጥ በረከት አለ - ሚል 3፡8-10
የምንሰጥበት ምክንያት እና አላማ
ሀ. እግዚአብሔር እንድንሰጥ አዟል - ዘፀ 25፡1-5፣ ዘሌ 25፡31፣ ዘኁ 18፡21
ለ. ስጦታችን የእግዚአብሔርን መንግስት የማስፋፋት ስራና የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ የሚውል ነው - 1ቆሮ 9፡4-14፣ 2ቆሮ 8፡4፣ ፊሊ 4፡15-18
ሐ. በመስጠት እግዚአብሔርን እናከብራለን፣ እናመልካለን - ምሳ 3፡9-10
መ. በመስጠት የእግዚአብሔርን በረከት እንለማመዳለን - ሚል 3፡10-12፣ ሉቃ 6፡10
ሠ. በመስጠት ለእግዚአብሔር ታማኝ እንሆናል (አንሰርቀውም) - ሚል 3፡8-10
እንዴት መስጠት እንዳለብን?
ሀ. የምንሰጠው አስቀድመን ራሳችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት ነው - ሮሜ 12፡1፣ 2ቆሮ 8፡1-5
ለ. የምንሰጠው በሃዘን (በግድ) ሳይሆን በደስታ ነው - 2ቆሮ 9፡7
ሐ. የምንሰጠው እንደገቢያችን ብቻ ሳይሆን ከጉድለታችንም ጭምር መሆን አለበት - 2ቆሮ 8፡1-5
መ. የምንሰጠው ለሰዎች ለመታየት መሆን የለበትም - ማቴ 6፡1
ሠ. የምንሰጠው በስጦታችን ለመመካት መሆን የለበትም - ሉቃ 18፡9-14
