የኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
.jpg)
አሁን በመላው አውሮፓ፥ በአፍሪካ፥ በአሜሪካ፥ በካናዳና በአውስትራልያ ከተቋቋሙት ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የመጀመሪያው ቀዳማዊና ፋና ወጊው ቤተ ክርስቲያን የኮሎኝ ርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነው። ቤተ ክርስቲያናችን በሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ፊት አውራሪነት፥ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አባታዊ ፈቃድ በዚያን ጊዜ በጅቡቲና በምሥራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ በነበሩት፥ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የኖርዲክ እና ግሪክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኾኑተ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ተባርኮ ተከፈተ።
አመሠራረቱም እንደሚከተለው ነው። በ 1971 ዓም ለሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ እና ዲያቆን በዕደ ማርያም መርሻ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፈቃድ ወደ ጀርመን ለከፍተኛ ትምህርት ተላኩ። ወደ ጀርመን ሀገር በገቡ በሁለት ዓመት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም ጽንሰ ሀሳቡ በመርህ ደረጃ ለውይይት ቀረበ። በሃይደልበርግ ኗሪ ከሆኑ ወንድሞች ጋር በእመቤታችን ቅድስት ማርያም የጽዋ ማኅበር ስም መሰባሰብ ጀመሩ። ማኅበሩ የመገናኛ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግላቸው ችሏል። በተለይም በ 1973 ዓ.ም. በምድረ ጀርመን በሃይደልበርግ ከተማ የመጀመሪያው ቅዳሴ ተቀደሰ። ለምእመናንም ቡራኬ ተሰጠ። በዚህም መንፈሳዊ አገልግሎት በለንደን ለጃማይካውያን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ተመድበው የነበሩት አባ አረጋዊ ወልደ ገብርኤል በኋላ የመላው አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ተገኝተዋል። ሥርዓተ ቅዳሴውንም መርተዋል። ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ካላቸው ፍቅርን ከተላበሰ ሰብእነታቸው የተነሣ መልካም ግንኙነት ነበራቸው። ቤተ ክርስቲያኑ ሲቋቋምም በበዓሉ ላይ ቤተ ክርስቲያናቸውን ወክለው ተገኝተዋል። የመጀመሪያው ቅዳሴ ከተካሄደ በኋላ ቤተ ክርስቲያን የማቋቋሙ ፍላጎት እየተጠናከረ መጣ። በሃይደልበርግና በሌሎች ከተማዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተካፋዮች የሆኑባቸው የዘመን መለወጫ፥ የልደትና የትንሣኤ በዓላት ይከበሩ ጀመር።
ከዚህ በኋላ ሁኔታዎች ሁሉ መልክ መልክ መያዝ ጀመሩ። የምእመናኑም ቁጥር እየጨመረ ሄደ። በአውሮፓውያኑ የሰማኒያዎቹ ዓመታት ላይ አያሌ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወደ ጀርመን በብዛት የገቡበት ጊዜ ነበር። በተለይም " Landesarbeitsgemeinschaft Ausländische Flüchtlinge Nordrhein-Westfalen in Düsseldorf e.V." የሚባል በመንግሥት በጀት የሚደጎም ማኅበር ተቋቁሞ የስደተኞችን ጉዳይ ይከታተል ስለነበር የኢትዮጵያን ስደተኞች የሚመለከት ዐውደ ጥናት ከመሰረም 8-11፥1973 በዱስልዶርፍ ከተማ ተካሄደ። የቤተ ክርስቲያናችን መሥራቾችም ከፕሮፌሰራቸው ከዶ/ር ሃየር ጋር ጸሎት እንዲያደርጉና ትምህርት እንዲሰጡ ተጋበዙ። የእሁዱ መርሃ ግብር የእኛ ብቻ ነበር፧ በጀርመንኛ ለሚቀርበው ጥያቄ በመምህራቸው እየታገዙ፧ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ችለዋል። ከሀገሩ ከወጣ በኋላ እንድ ቀን እንኳ ቃለ እግዚአብሔር ሰምቶ ያማያውቀው ሁሉ ያነባ ነበር። በተለይ ፕሮፌሰር ሃየር እኛን ለመርዳት ቆርጠው የተነሡት የዚያን ሕዝብ ስሜት ከተመለከቱ በኋላ ነበር ማለት ይቻላል።
ቤተ ክርስቲያን ለምን አናቋቁምም የሚለው ጥያቄ የዕለት ከዕለት ጥያቄ ሆኖ መቅረብ ጀመረ። ለዚህም አንድ አመች ዕድል ተፈጠረ። ከላይ በተጠቀሰው በ 1973 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ባደረገችላቸው ጥሪ መሠረት ጀርመንን ሲጎበኙ፥ ቤተ ክርስቲያን እድናቋቁም ፈቃዳቸው ይሆን ዘንድ ፍራንክፈርት ላይ ጥያቄ ቀረበ። ቅዱስነታቸውም ጥቂት ካሰቡ በኋላ ተማሪዎቹን ካህናት «ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ለምን ወደ ሀገራችሁ አትመለሱም» አሉዋቸው። እነርሱም «ቅዱስ አባታችን ከሀገሩ የወጣው ሕዝብ ብዙ ስለሆነ፧ እንደሌሎቹ ኦርቶዶክሳውያን የእኛም አማንያን ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋቸዋል» የሚል መልስ ሰጡ። አስከትለዋቸው የመጡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ አቡነ ኤልያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ተከታትለው የጨረሱ፧ በዝርዎት ያሉትን የግሪካውያንንና የሌሎቹንም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታ ስለሚያውቁ ለሀሳቡ ላይ ድጋፍ ሰጥተዋል። በመጨረሻም «ለማናቸውም ደብዳቤ ጻፉ» ብለው ካረፉበት ክፍል ቡራኬ ተቀብለው ወጡ።
ቤተ ክርስቲያናችን በታሪክ ውስጥ
የመጀመሪያው 10 አመታት
1. ከአገር ቤት ለትምህርት የመጡ ሁለት መንፈሳዊ ተማሪዎች፡፡ 2. የመጀመሪያው ቅዳሴ በሃይድል በርግ (ሊ. ካ, መርዓዊ ተበጀ እና ቀሲስ ዘለአለም) 3. ፓትረያሪክ ብፁህ አቡነ ተክለ ሐይማኖት ጀርመን ሀገር ለጉብኝት በመጡበት ወቅት፣ የመጀመሪያው የቅዱስ ሚካኡል ቤተ ክርስትያን እንዲከፈት ሊካ መርዓዊ ተበጀ ፍቃድ ሲጠየቁ፣ 4. የመጀመሪያው የሰበካ ጉባኤ ምስረታ እና ስብሰባ። 5. በ 1981-1983 በጀርመን ሐገር ውስጥ የመጀመሪያው የቅዱስ ሚካኤል መንፈሳዊ አግልግሎት። ከ1983-1985 ከሃይድልበርግ እየተመላለሱ ሲያገለግሉ፡፡ ሊ. ካ. መርዓዊ ተበጀ 6. ሊ.ካ.መርዓዊ ተበጀ ሌሎችን ካህናት በማስተባበር ከኮሎኝ በመነሳት በጀርመን እና በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ፡፡ 7. በጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ WDR ግብዣ የመጡ የቅዱስ ያሬድ ዘማሪያን በኮኒቨርት ቤተክርስትያን ዝማሪ ሲያቀርቡ፡፡
ሁለተኛው 10 አመታት
1. በጀርመን አገር ባሉ አብያተ ክርስትያናት ስለ ኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገለፃ ሲደረግ፡፡ 2. የጀርመን አብያተ ክርስትያናት የሐይማኖት አባቶችን እና አገልጋዬች በኢትዬጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ፡ 3. በጀርመን አገር ያሉ ቤተክርስትያኖች የሚገናኙበት ቀን (Kirchen Tag) ላይ ተሳትፎ ሲደረግ:: 4. በኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በአመታዊ የካህናት ስብሰባ ላይ አመታዊ ሪፖርት ሲያቀርቡ፡፡
የሶስተኛው 10 አመታት
1. ቀድሞ ከኢቫንጌሊሽ ቤተክርስትያን መልካም ፍቃድ በጊዚያውነት የተሰጠውን ቤተክርስትያን ግዢ የተፈፀመበት። 2. የቤተክርስትያን እድሳት ሲደረግ 3. የመዘምራን አገልግሎት 4. የ 25 አመት ክብረ በአል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር 5. የ 30 አመት ክብረ በአል
የመጨረሻው 10 አመታት
1. የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች፡ 2. በኮሮና ጊዜ ያልተቋረጠ አገልግሎት 3. ተጨማሪ ቤት እና ቦታ ግዢ
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር
አስተዳዳሪ
ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ
አሁን ያሉ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር (2016-2019 ዓ.ም.)
ወይዘሪት ሒሩት መለሰ
አቶ ታመነ መልአኩ
አቶ ቴዎድሮስ ሣህሉ
አቶ በላይ ሶሎሞን
አቶ ይበልጣል
አቶ ወንድም
ወይዘሮ መሠረት
ወይዘሮ ዮርዳኖስ
